በአንድ ሀገር ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ሲካሄድ የተለያዩ መስፈርቶችን ማሟላት እንደሚጠበቅበት እሙን ነው፡፡ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ስንል መሰረታዊ የዓለም ዓቀፍ የዴሞክራሲያዊ ምርጫ ሂደትና መርህ ያሟላ መሆን ይኖርበታል፡፡ መሰረታዊ የዓለም ዓቀፍ ሂደቶችና መርሆዎችን ሲባል በመጀመሪያ ደረጃ አገሪቱ ሕገመንግስት ሊኖራት ይገባል፡፡ በሕገመንግስቱ እውቅና ያገኘ ገለልተኛ የምርጫ ኮሚሽን መኖር እንዳለበት፣ በየስንት ዓመት መካሄድ እንዳለበት፣ በዚህ መሰረትም ተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአገሪቱ ሕግ መሰረት ጨዋታቸውን እንደሚያካሂዱ ያስቀምጣል፡፡ ምርጫ ተጠናቆ አሸናፊ የሆነው ፓርቲ በገለልተኛ የምርጫ ኮሚሽን ወይም ቦርድ ይፋ ከሆነ በኋላ በአጭር ጊዜ ውስጥ የድህረ ምርጫ ዳሰሳ ጥናት ማካሄድ እንደ አንድ ዓለም አቀፍ መለኪያ (Standard) ይወሰዳል፡፡
ሀገራችን ኢትዮጵያ የ2002 ጠቅላላ ምርጫ ፍትሃዊ፣ ነፃ፣ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ እንዲሁም በህዝባችን ዘንድ ተአማኒ የሆነ ምርጫ ማካሄዷ ይታወቃል፡፡ ይህ አንደተጠበቀ ሆኖ ከምርጫው በኋላ የዳሰሳ ጥናት በማካሄድ በሂደቱ የነበሩ ጠንካራና ደካማ ጎኖችን መፈተሽ ያስፈልጋል፡፡ ይህንን ለማወቅ ቦርዱ በሀገሪቱ የምርጫ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የድህረ ምርጫ ግምገማ አካሂዷል፡፡
የግምገማ ጥናቱ በኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ባለቤትነት የተከናወነ ሲሆን ዓላማውም በሀገራችን ለአራተኛ ጊዜ በተካሄደው ጠቅላላ ምርጫ ወቅት የታዩ ደካማና ጠንካራ ጎኖችን ለይቶ በማውጣት ወደፊት ለሚካሄዱ ህዝባዊ ምርጫዎች ካለፉት በተሻለ ሁኔታ ነጻ፣ ፍትሃዊ፣ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ እና ታዓማኒ እንዲሆኑ፣ ደካማ ጎኖችን ለማረምና ጠንካራ ጎኖችን አጠናክሮ ለመቀጠል ነው፡፡
ለዚህ ጥናት የሚያስፈልጉ መጠይቆች ከስታስቲክስ ባለስልጣን በመተባበር ተቀባይነት ባለው ሳይንሳዊ መንገድ የፅሑፍ መጠይቆች (Questionnaire) በማዘጋጀት መላሾቹ በቀላሉ ሊረዱትና ሊመልሱት በሚችሉበት መልኩ ነበር የተቀረፀው፡፡
በመጠይቆቹ የተካተቱት ዋና ዋና ነጥቦች በምርጫ ጣቢያና በምርጫ ክልል ጽ/ቤቶች አደረጃጀት፣ ተደራሽነትና ደህንነት፣ የመራጮችና የእጩዎች ምዝገባ ሂደት፣ የስነ ዜጋና የመራጮች ግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት፣ የመምረጥ መብትና የሴቶች የምርጫ ተሳትፎ፣ የምርጫ አስፈጻሚዎች ብቃትና ገለልተኝነት፣ የቦርዱና የባለድርሻ አካላት የስራ ግንኙነትና የመረጃ ልውውጥ፣ የምርጫ ቅስቀሳ፣ የቅሬታ አቀራረብ፣ የምርጫ ህግ፣ የድምጽ አሰጣጥ፣ ቆጠራና ውጤት አገላለጽ ወዘተ… ናቸው፡፡
በዚህ በ2002 ዓ.ም ድህረ ምርጫ ግምገማ ላይ ከዘጠኙም ብሔራዊ ክልሎችና ከሁለቱ የከተማ መስተዳደሮች ስር ከሚገኙ 77 ዞኖች መረጃዎቹ የሳይንሳዊ ናሙና መርሆዎች (Statistical Sampling Method) በመከተል የተሰበሰቡ ናቸው፡፡ በዞኖቹ ስር በናሙናነት በተመረጡ 154 የምርጫ ክልሎችና በ916 የምርጫ ጣቢያዎች ከሚገኙ መራጮች፣ የምርጫ አስፈጻሚዎች፣ የህዝብ ታዛቢዎች፣ በየደረጃው ከሚገኙ የፍትህ አካላት፣ የአስተዳደር አካላት፣ የመገናኛ ብዙኃን፣ የሲቪል ማህበራት እና የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮችን ከሚወክሉ አስራ ስምንት ሺህ ስምንት መቶ ሰማኒያ አንድ የህብረተሰብ ክፍሎችን አስተያየት በጽሑፍ መጠይቅ ተሰብስቧል፡፡
ይህ የባለድርሻ አካላት በነፃነት የሞሉት መጠይቅ ከሀገሪቱ ሁሉም ክልሎች ተሰብስቦ በስታስቲክስ ባለሙያዎች አግባብነት ባለው የስታትስቲክስ ሶፍትዌር Statistical Package for the Social Sciences (SPSS) ተጠናቅሯል፡፡ ቦርዱ የግምገማ ውጤቱ ከተጠናቀረ በኋላ ረቂቁን አዘጋጅቶ ባለድርሻ አካላትን በማወያየት አስተያየቶችን በመቀበል እንዲዳብር አድርጓል፡፡
የድህረ ምርጫ ግምገማው ፍይዳ ቦርዱ የመራጩን ህዝብ ፋላጎት ተገንዝቦ የምርጫ አሰራርን በማሻሻል ተሳትፏቸው አሁን ካለበት ይበልጥ እንዲጨምር፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳትፎ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ያስችላል፡፡ በተጨማሪም አለም አቀፍ የምርጫ መርሆዎችን በማሳካት የሀገራችን ዲምክራሲያዊ ሂደት እንዲጎለብት ያደርጋል፡፡
በመሆኑም የተጠናቀረው የግምገማ ውጤት በ2002 ዓ.ም ጠቅላላ ምርጫ የነበረውን ደካማና ጠንካራ ጎኖችን ለማወቅ፣ በምርጫ ሕጉና አፈፃፀሙ ላይ የታዩ ክፍተቶችን ለመለየት የሕግና አሰራር ማሻሻያዎችን እንዲጠቁም እንዲሁም ከጥናቱ በመነሳት ቀጣይ ስትራተጂ ለመቅረፅ ትልቅ ዓቅም ፈጥሯል፡፡
በቦርዱ ካሉት እሴቶች አንዱ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀራረብ በመደማመጥና በመወያየት እንዲሁም አግባብነት ያላቸው ሃሳቦች በመቀበል ጠንካራ የሆኑትን በበለጠ ማጠናከር የሚያጋጥሙ ክፍተቶችን ማስተካከል ነው፡፡ ባለፉት ዓመታት ውስጥ በሚወጡ ደንቦችና መመሪያዎች፣ መንግስት ለፖለቲካ ድርጅቶች የሰጠው የፋይናንስ ድጋፍና የአየር ሰዓት አጠቃቀም፣ የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ እና በመሳሰሉት ጉዳዮች ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በመመካከርና በመወያየት ተግባራዊ ማድረጉ ቦርዱ ከባለድርሻ አካላት ጋር ያለው ግንኙነት ምን ያህል ጠንካራ መሆኑን መገመት ይቻላል፡፡
የ2002 ዓ.ም ድህረ ምርጫ ግምገማም በቦርዱ ፅ/ቤት ያሉትን ጥንካሬዎች፣ ድክመቶች፣ ተግዳሮቶችና ዕድሎች የሚያውቅበት ያሉትን ጥንካሬዎች የሚያስቀጥልበት፣ ድክመቶችን የሚያሻሽልበት፣ ዕድሎችን (Opportunities) አሟጦ የሚጠቀምበት፣ ሊከሰቱ የሚችሉ ተግዳሮቶች (Challenges) የሚቀንስበት ነው፡፡ ስለሆነም ለወደፊት የሚካሄዱትን ምርጫዎች ካለፉት በበለጠ መልኩ ነፃ፣ ፍትሃዊ፣ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ እንዲሁም በህዝብ ዘንድ ተዓማኒ እንዲሆን ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖረዋል፡፡
አገራችን ላለፉት ሰባት ተከታታይ ዓመታት ሁለንተናዊ ዕድገት ማስመዝገቧ የሚታወቅ ነው፡፡ ይህንን ይበልጥ ለማጠናከር መንግስት የአምስት ዓመቱ የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አዘጋጅተዋል፡፡ ይህንን ዕቅድ ለማሳካት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተጣለበትን ሃላፊነት በበለጠ መልኩ ያጠናክር ዘንድ የ2002 ዓ.ም የድህረ ምርጫ ግምገማ ውጤት ትልቅ አስተዋፅኦ አለው፡፡
No comments:
Post a Comment