ሀገራችን ኢትዮጵያ ከ1983 ዓ.ም ድረስ በተማከለ የፖለቲካ ስርዓት ትተዳደር ሥለነበር ዜጎች የፈለጉትን አስተሳሰብ ይዘው የፖለቲካ ድርጅት በማቋቋም የሚንቀሳቀሱበት ህጋዊ ስርዓት የተፈቀደ አልነበረም፡፡ ይህ ዓይነቱ ስርዓት ባለመፈጠሩ ሀገሪቱ ለብዙ ዓመታት የዘለቀ የእርስ በርስ ጦርነት ስታስተናግድ ቆይታለች፡፡ እንደዚህ ዓይነቱ ችግር የሚፈታው የሐሳብ ልዩነትን የሚያስተናግድ የመድበለ ፓርቲ ስዓርት ሲኖር ብቻ ነው፡፡ የመድበለ ፓርቲ ስርዓት በሀገራችን የተጀመረው ግንቦት 2ዐ ቀን 1983 ዓ.ም. ወዲህ በደርግ ውድቀት ማግስት ነው፡፡ የደርግ መንግሥት መገርስን ተከትሎ በተፈጠረው የዲሞክራሲ ፍንጭ በመጠቀም በሀገር ውስጥ እና በውጭ ያሉ የነፃነት እንቅስቃሴ የሚያካሂዱ የፖለቲካ ድርጅቶች ተሰባስበው የሽግግር መንግሥት በመመስረት እንደ ህገ መንግስት የሚያገለግል የሽግግር ቻርተር አፀደቁ ፡፡ የሽግግር ቻርተሩን ተመስርቶ በሀገሪቷ የተለያየ አስተሳሰብ ያላቸው የፖለቲካ ድርጅቶች አማራጫቸውን ለህዝቡ አቅርበው መወዳደር የሚችሉበትን የተደላደለ ሜዳ የሚፈጥርና የምርጫ እንቅስቃሴን በገለልተኝነት የሚመራ ተቋም ማቋቋም አስፈላጊ በመሆኑ የምርጫ ኮሚሽን በአዋጅ ቁጥር 11/1984 ተቋቋመ፡፡ የምርጫ ኮሚሽን ተልዕኮውን ጨርሶ በአዋጅ ሲፈርስ በምትኩ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የምርጫን ስራ በገለልተኝነት የማስፈፀም ተልዕኮ ተሰጥቶት ተተካ፡፡
አሁን በሥራ ላይ ያለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በተሻሻለው የምርጫ ህግ ቁጥር 532/1999 ዓ.ም. ተቋቁሞ፣ ሁሉንም የፖለቲካ ፓርቲዎች በገለልተኝነት፣ በእኩልነትና በታማኝነት እያገለገለ የምርጫ እንቅስቃሴዎችን በብቃት እየመራ ይገኛል፡፡ የሀገራችንን መድበለ ፓርቲ ስርዓት እንድጎለብት እና የውድድር ሜዳው የተመቻቸ እንዲሆን ቦርዱ ባወጣቸው ከ 16 በላይ ለምርጫ አፈጻጸም የሚረዱ ደንቦችና መመሪያዎች ፖለቲካ ፓርቲዎችን እና ሌሎች ከባለድርሻ አካላት በማማከርና ጠቃሚ አስተያቶቻቸውን በማካተት በስራ ላይ እንድውሉ በመደረጉ የምርጫ አፈጻጸማችን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ እንዲመጣ አግዟል፡፡ በተጨማሪም ከባለድርሻ አካላት ጋር በመመካከር አቅማቸው እንድጎለብት የስልጠና፣ አውደ ጥናትና የውይይት መድረኮችን በማመቻቸት በርካታ የአቅም ግንባታ ስራዎችን ሰርቷል፡፡
በመሆኑም ሀገራችን ኢትዮጵያ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ማካሄድ ከጀመረች ሁለት አሥርት ዓመታትን አሳልፋለች፡፡ በነዚህ ዓመታቶች ሥርዓቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል፣ ዜጐች በፈለጉት የፖለቲካ አስተሳሰብ ተደራጅተው መንቀሳቀስ እንዲችሉ ተደርጓል፡፡ በሽግግር መንግስት ወቅት እና ከ1987 ዓ.ም እስከ 2003 ዓ.ም. በተካሄዱ የጠቅላላ፣ የአካባቢ፣ የማሟያ ምርጫዎች እና የህዝበ ውሳኔዎች የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች በየጊዜው ተሳትፎአቸው እያደገ የመጣበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡
መንግስት በፓርላማ መቀመጫ ካላቸው ፓርቲዎች ጋር በሚወጡ ህጎች እና አዋጆች ላይ ቀድሞ እየተወያየ በህዝብ ተዎካዮች ምክር ቤት ጸድቀው እንድወጡ እያደረገ ይገኛል፡፡ በተጨማሪ ለፖለቲካ ፓርቲዎች የፋይናንስ ድጋፍ በማድረግ ቁርጠኝነቱን አሳይቷል፡፡ ቦርዱ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር እየተመካከረና እየተወያየ እንደሚሰራ ሁሉ፣ በ 2003 በጀት ዓመትም ይህንኑ አጠናክሮ በማስቀጠል፤ በማሟያ ምርጫ፣ በ2002 ድህረ ምርጫ ዳሰሳ ጥናት ላይ ውይይትና ምክክር እንዲሁም በምርጫ ህጉ፣ በፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ፣ በመንግስት የፋይናንስ ድጋፍ አጠቃቀም እና በሁለንተናዊ አመራር ላይ ስልጠና በመስጠት አቅማቸው እንድጎለብት አድርጓል፡፡ ይህ የመንግስትና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያልተቋረጠ ጥረት ይበልጥ የፖለቲካ ምህዳሩ እንዲሰፋና ሁሉም ህጋዊና ሰላማዊ ፖለቲካ ፓርቲዎች በእኩልነት እና በፍትሃዊነት እንድንቀሳቀሱ ለማስቻል ነው፡፡
የአገራችን መድብለ ፓርቲ ሥርዓት ተጠናክሮ፣ ዴሞክራሲ ሥርዓቱ ይበልጥ እንዲጐለብት እና የፖለቲካ ፓርቲዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የፋይናንስ አቅም እንዲኖራቸው ያስፈልጋል፡፡ የፋይናንስ አቅም ሲኖራቸው አባሎቻቸውንና ደጋፊዎቸውን ለማንቀሳቀስ እድል ይሠጣቸዋል፡፡ ለፖለቲካ ፓርቲዎች ዋናው የፋይናንስ ምንጭ ሆኖ የሚያገለግለው ከአባሎቻቸውና ከደጋፊዎቻቸው የሚሠበሰቡት ገንዘብ ቢሆንም ከዚህ በተጨማሪም የአገሪቱ የኢኮኖሚ አቅም በፈቀደው መልኩ ቦርዱ ከመንግሥት በጀት በማስፈቀድ የገንዘብ ድጐማ ይሠጣቸዋል፡፡ ከመንግሥት የሚሠጠው የገንዘብ ድጐማ በፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ ቁጥር 573/2000 ዓ.ም አንቀጽ 42 ንዑስ አንቀጽ 1 እና አንቀጽ 45 ንዑስ አንቀጽ 1 መሠረት ለፖለቲካ ፓርቲዎች የሚሠጠው ድጋፍ በፌዴራል ወይም በክልል ምክር ቤቶች ባላቸው መቀመጫ ብዛት መሠረት እንደሆነ ተደንግጓል፡፡ ከመንግሥት ለፖለቲካ ፓርቲዎች የሚሠጠው ድጋፍ በምርጫ ወቅትና ከምርጫ ውጭ በየዓመቱ ለዕለት ከዕለት ተግባራት ማከናወኛ የሚውል ነው፡፡ በመደበኛነት በየዓመቱ የሚጠው የገንዘብ ድጐማ በምርጫ ወቅት እንደማይሠጥ እና የራሱ የምርጫ ድጐማ ብቻ እንደሚሠጥ በአዋጁ ተደንግጓል፡፡
በዚህ መሠረት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አዋጁ ከወጣ በኋላ በ2002 ዓ.ም. ለምርጫ ሥራ የሚውል ከመንግሥት የተመደበን ገንዘብ ለ63 ተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በተቀመጠ የክፍፍል ቀመር መሠረት እንዲከፋፈሉ አድርጓል፡፡ በበጀት ዓመቱም ለመደበኛ የዕለት ተዕለት ተግባራትን የሚያከናውኑበት 10 ሚሊዮን ብር ከመንግሥት በጀት አስፈቅዶ እንደተለመደው ፖለቲካ ፓርቲዎች በክልልና በፓርላማ ባላቸው መቀመጫ ብዛት ህጉን ተከትሎ አከፋፍሎ እየተጠቀሙ ይገኛሉ፡፡ መንግሥት በሠጠው የገንዘብ ድጐማ ተጠቃሚ የሆኑት 8 የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ ያላቸው እና 9 የክልል ም/ቤቶች መቀመጫ ያላቸው ፖለቲካ ፓርቲዎች ናቸው፡፡
ቦርዱ ከመንግሥት አስፈቅዶ ለፖለቲካ ፓርቲዎች የሠጠው የድጐማ ገንዘብ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓቱን ለማጠናከር እና የአገራችን ዴሞክራሲ የላቀ ደረጃ እንዲደርስ ታሳቢ ያደርገ ነው፡፡ በመሆኑም ገንዘቡን የወሰዱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የፓርቲያቸውን የዕለት ተዕለት ተግባር፣ የህዝቡን የፖለቲካ ግንዛቤ በማዳበር፣ ዜጐች የሀገሪቱ ፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ ንቁ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ማድረግ፣ የፓርቲያቸውን ዓላማ ማስረፅን፣ በህዝቡና በመንግሥት ተቋማት መካከል መልካም ግንኙነት እንዲፈጠር የማድረግ ተግባራትን እንዲያከናውኑበት የተሰጠ ድጋፍ ለተባለለት ዓላማ አውለው መገኘት የሚኖርባቸው ሲሆን ቦርዱም በወቅቱ ተጠቅመው እንዲያወራርዱ የመከታተል ኃላፊነቱን ይወጣል፡፡
ጠቅላላ የገንዘቡ ድጋፍ ለጠቅላላ መቀመጫ ብዛት ተካፍሎ የተገኘው ገንዘብ መጠን የአንድ ወንበር ዋጋ ይሆናል፡፡ በዚሁ መሠረት ፖለቲካ ፓርቲዎች ባገኙት መቀመጫ መጠን ተሠልቶ ተከፋፍሏል፡፡ በአጠቃላይ ይህ የፋይናንስ ድጋፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተጨማሪ አቅም አግኝተው እንዲንቀሳቀሱ የውድድር መድረክ የሚከፍት ነው፡፡ ከመንግሥት ለፖለቲካ ፓርቲዎች የሚጠው የገንዘብ ድጋፍ የአገሪቱ የኢኮኖሚ አቅም በፈቀደ መልኩ ቀጣይነት ያለው በመሆኑ ወደፊትም ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡
No comments:
Post a Comment