ምርጫ የአንድ ሀገር ህዝብ የሉዓላዊነት መገለጫ ነው፡፡ ህዝቦች በነፃነትና በቀጥታ በመሳተፍ ያስተዳድሩኛል ብለው ያመኑባቸውን ወኪሎቻቸውን የሚመርጡትና ፈቃዳቸውን የሚገልፁት በምርጫ ብቻ ነው፡፡ በሀገራችን ምርጫን የማስፈፀም ሥልጣንና ኃላፊነት በህገ መንግሥቱ አንቀጽ 102 መሰረት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ተሰጥቷል፡፡ በተጨማሪም በተሻሻለው የምርጫ ህግ 532/1999 ዓ.ም. መሠረት አምስት የምርጫ ዓይነቶች መኖራቸው የተገለፀ ሲሆን እነሱም፡- የጠቅላላ፣ የአካባቢ፣ የማሟያ፣ የድጋሚና የህዝበ ውሳኔ ምርጫዎች ናቸው፡፡
ከእነዚህ የምርጫ አይነቶች አንዱ የማሟያ ምርጫ ሲሆን የማሟያ ምርጫ በይውረድልን ወይም በማንኛውም ምክንያት በየደረጃው የሚገኙ የተጓደሉ የምክር ቤት አባላት መቀመጫዎችን ለማሟላት የሚካሄድ የምርጫ ዓይነት ነው፡፡ በተሻሻለው የምርጫ ህግ ቁጥር 532/1999 ዓ.ም. አንቀጽ 30 መሠረት የማሟያ ምርጫ የሚካሄደው በየደረጃው ያሉ ምክር ቤቶች በተለያዩ ምክንያት የተጓደሉባቸውን አባላት እንዲሟሉላቸው ለቦርዱ ጥያቄ ሲያቀርቡ ወይም በህጉ መሠረት የቀረበ የይውረድልን ጥያቄ ተቀባይነት ሲያገኝ ቦርዱ ጥያቄው በደረሰው በ3 ወር ጊዜ ውስጥ የማሟያ ምርጫ ያካሂዳል፡፡ ሆኖም አንድ ምክር ቤት የሥራ ዘመኑ ሊያልቅ 6 ወር የቀረው ከሆነ የማሟያ ምርጫው እንደማይካሄድ በዚሁ አንቀጽ ተደንግጓል፡፡
የማሟያ ምርጫ አፈፃፀም
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተጣለበትን ህገ መንግሥታዊ ኃላፊነት ለመወጣት በተለያዩ ጊዜያት የተካሄዱ የተለያዩ ምርጫዎችን ነፃና ገለልተኛ ሆኖ በብቃት እያስፈፀመ የመጣ፣ አቅምና ልምድ ያካበተ ተቋም ነው፡፡ በ1994፣ በ1990 እና 2001 ዓ.ም በተለያዩ የአገራችን አካባቢዎች የቀረበለትን ጥያቄ ተቀብሎ የተረጋጋ፣ ሰላማዊ፣ ነፃና ፍትሃዊ የማሟያ ምርጫ አካሂዷል፡፡ በተመሳሳይ በዚህ በ2003 የበጀት ዓመትም የህዝቡን የዕለት ተዕለት አስተዳደራዊ ጉዳዮችን በቅርበት ለመፍታት የሚችሉ የምክር ቤት አባላት እንዲሟሉ የሚደረግበትን የማሟያ ምርጫ፣ በህጉ መሠረት ከኦሮሚያ ክልል፣ ከደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል እና ከአዲስ አበባ አስተዳደር ምክር ቤቶች የቀረበለትን ጥያቄ መርምሮ የምክር ቤቶቹ ቀሪ የሥራ ዘመን ከ6 ወር በላይ መሆኑን በማረጋገጥ የማሟያ ምርጫውን በነፃ፣ ፍትሃዊነትና በሰላማዊነት አካሂዷል፡፡ የማሟያ ምርጫ በየደረጃው የሚገኙ የምክር ቤት አባላት የህዝቡን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮች በቅርበት በሙሉ አቅማቸው መወሰንና ተግባራዊ ማድረግ እንዲችሉ እድል የሚሠጥ ነው፡፡ በተለይም የወረዳና የቀበሌ ምክር ቤቶች የህዝቡን አስተዳደራዊ ችግሮች በቀጥታና በቅርበት ተገኝተው የሚፈቱበት በመሆኑ ህዝቡ በዚህ የማሟያ ምርጫ ከምዝገባ እስከ ምርጫው ቀን ድረስ በንቃት በመሳተፍ ወኪሎቹን መምረጥ ችሏል፡፡
ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለማሟያ ምርጫ የሚሰጡት ትኩረት አናሳ መሆኑ በሂደቱ ለመገንዘብ ተችሏል፡፡ የማሟያ ምርጫ ደግሞ ወደፊትም ጥያቄ ሲቀርብ የሚካሄድና የቦርዱ መደበኛ ስራ ሆኖ የሚቀጥል ነው፡፡ በመሆኑም ቦርዱ ይህንን ታሳቢ በማድረግ ችግሩን ለማሻሻልና ወደፊት በሚካሄዱ ምርጫዎች ፖለቲካ ፓርቲዎች እና ሕዝቡ ይበልጥ በንቃት ለመሳተፍ የሚያስችላቸውን የመራጮችና ሥነ ዜጋ ትምህርት ከወዲሁ ለመስጠት ዝግጅቱን አጠናቌል፡፡
No comments:
Post a Comment