የዴሞክራሲ ፅንሰ - ሃሳብ አንድን ማህበረሰብ በጋራ ተጠቃሚ የሚያደርግ ወይም ለማህበረሰቡ ጉዳት ሊያስከትል በሚችል ጉዳይ ላይ የማህበረሰቡ አባላት በሚያደርጉት የጋራ ውይይት ችግሩን የሚፈቱበት እና እያንዳንዱ ተወያይ እኩል ተደማጭነት የሚያገኝበት ሆኖ በሚቀርቡ የመፍትሔ ሃሳቦች ላይ ጥቂቶቹ የአብዛኛውን አማራጭ ሃሳብ በማክበር ወደ ተግባር የሚለወጥበት ሥርዓት ነው፡፡ ሂደቱ ጥቂቶች የሚደመጡበት፣ የብዙሃን ድምፅ የሚከበርበት እና የአባላት ድምፅ እኩል የሆነበት ነው፡፡
ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚገለጽበት ዋንኛ መንገድ ምርጫ ነው፡፡ ምርጫ ለህዝብ የቆመ እና የዜጐች ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የሚከበርበት መንግሥታዊ ሥርዓት እንዲኖር ከሚያደርጉ የሉዓላዊነት መገለጫዎች አንዱ እና ዋነኛው ነው፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ የመንግሥታዊ ሥልጣን ምንጭ ህዝቡ መሆኑና የመንግሥት ተጠያቂነትም ለህዝብ መሆኑ ነው፡፡ ስለሆነም ህዝቡ ይህን ታላቅ ሀገራዊ ኃላፊነቱን መወጣት እንዲችል ሥነ - ዜጋዊ እውቀት እና ክህሎት ማዳበር ይጠበቅበታል፡፡
አሁን በስራ ላይ ያለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰኔ 19 ቀን 1999 ዓ.ም ኃላፊነቱን ሲረከብ ጽ/ቤቱ ያለበትን ችግር በጥናት ለይቶ እና የመፍትሄ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ ነበር ወደ ስራ የገባው፡፡ በችግርነት ከተለዩትና መፍትሄ ከሚያስፈልጋቸው መካከል የመራጮችና የስነ-ዜጋ ትምህርት አሰጣጥ ሁኔታ አንዱ እና ዋነኛው ነበር፡፡ ቦርዱ ለችግሩ መፍትሄ ለመስጠትም ከሁለት አመት በላይ ጊዜ ወስዶ የመራጮችና የስነ-ዜጋ ትምህርት ማስተማሪያ ማኑዋል ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በጥንቃቄ አዘጋጅቷል፡፡ ይህ ማስተማሪያ ማኑዋል በቦርዱ ፀድቆ ተግባራዊ እንዲሆን ተወስኗል፡፡
ቦርዱ የተጣለበትን ምርጫ የማስፈፀም ታላቅ ሃገራዊ አደራ ለመወጣት ባለፉት 4 ዙሮች ባካሄዳቸው የጠቅላላ እና የአካባቢ ምርጫዎች ህዝቡ በእውቀት ላይ የተመሠረተ ምርጫ ማከናወን እንዲችል ልዩ ልዩ ስልቶችን በመጠቀም በመላ ሀገሪቱ የመራጮችና የሥነ - ዜጋ ትምህርት በመሥጠት የህዝቡን ሥነ - ዜጋዊ እውቀትና ክህሎት ለማዳበር እና ለማሳደግ ባደረገው ጥረት፣ ህዝቡ በተለያዩ ዙሮች በተሳተፈባቸው ምርጫዎች በየጊዜው እየዳበረ የመጣ በእውቀት ላይ የተመሠረተ ምርጫ በማካሄድ አመርቂ ውጤት ለማየት የቻለበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡
ይህን የህዝቡ ሥነ - ዜጋዊ እውቀት እና ክህሎት በላቀ ደረጃ ማሳደግ እንዲቻል ቦርዱ በመላ ሀገሪቱ ጥቅም ላይ የሚውል፣ ወጥነት ያለው ይዘትና ስልትን አጠቃሎ የያዘ የመራጮችና የሥነ - ዜጋ ትምህርት ማስተማሪያ ማኑዋል አዘጋጅቷል፡፡ ይህ ማስተማሪያ ማኑዋል በ2002 ዓ.ም. በተደረገው ምርጫ ለማስተማሪያነት ጥቅም ላይ ውሎ ከፍተኛ ውጤት አስገኝቷል፡፡ በዚህ ዓመትም ይበልጥ በባለድርሻ አካላት ተገቢው ምክክር እና ውይይት ተደርጐበት ዳብሮ በማኑዋልነት በቦርዱ ፀድቋል፡፡
የማስተማሪያ ማኑዋሉ በሀገራችን ባሉ የክልሎች የሥራ እና የትምህርት ቋንቋዎች በመተርጐም ላይ ነው፡፡ ሁሉም ዜጐች ሥነ ዜጋዊ እውቀት እና ክህሎትን ማሳደግ እንዲችሉ እና ምክንያታዊ ሆነው የሚበጃውንና የሚጠቅማቸውን ለመምረጥ የሚያስችላቸው ግንዛቤ የሚያገኙበት ይሆናል፡፡
ቦርዱ ይህን ትምህርት ለመላው የሀገራችን ህዝብ እንዲዳረስ ለማድረግ ልዩ ልዩ ስልቶችን ቀይሶ ወደ ተግባር ገብቷል፡፡ በዚህ ረገድ የሚጠቀሰውና ወደ ሥራ የተገባበት የብሔራዊ እና ክልላዊ የመገናኛ ብዙሃንን ሬዲዮ በመጠቀም በልዩ ልዩ ቋንቋዎች ትምህርቱ ለህዝቡ እንዲደርስ ማድረግ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ቦርዱ ከአማራ ክልል መገናኛ ብዙሃን፣ ከኦሮሚያ ክልል መገናኛ ብዙሃን፣ ከሶማሌ ክልል መገናኛ ብዙሃን፣ ከአዲስ አበባ መገናኛ ብዙሃን፣ ከደቡብ ክልል መገናኛ ብዙሃን እንዲሁም ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እና ከትግራይ ድምፅ ወያኔ ሬዲዮ ጋር ማኑዋሉን ለማስተማር የሚያስችል ለአንድ ዓመት የውል ስምምነት ለመፈጸም ዝግጅቱን አጠናቋል፡፡
ለአንድ ዓመት በሣምንት ለሁለት ተከታታይ ቀናት ለሁለት ሰዓት በሬዲዮ የሚተላለፈው ትምህርት ለመገናኛ ብዙሃኑ በውሉ መሠረት ወጥነት ባለው መልኩ ትምህርቱ ሳቢ እና ማራኪ በሆነ መንገድ መሥጠት እንዲችሉ ቦርዱ ውል ለተዋዋሉት የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ሥልጠና ለመሥጠት ዝግጅቱን አጠናቋል፡፡ ከዚህ ሥልጠና በኋላም በሁሉም ክልሎች የመራጮችና የሥነ - ዜጋ ትምህርት በቋሚነት ይሠጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የሥነ - ዜጋ ትምህርት ዜጐች ስለ መንግሥት፣ ስለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት፣ ስለህዝብ የሥልጣን ባለቤትነት፣ ስለ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸው፣ ስለማህበራዊና ህገ - መንግሥታዊ መብትና ግዴታዎቻቸው፣ ስለ አካባቢ ልማት፣ ስለተፈጥሮ ሀብት፣ ስለ ድህነት ቅነሳ… ወዘተ ግንዛቤና እውቀት የሚያዳብሩበት ትምህርት ነው፡፡
ይህ ትምህርት ዜጐች በእውቀት ላይ የተመሠረተ ምርጫ እንዲያከናውኑ የሚረዳቸው ሲሆን ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማስመዝገብ፣ መልካም አስተዳደርን ለማስፈንና ብልሹ አሠራሮችን ለማስወገድ እንዲሁም የሚፈጠርባቸውን ወቅታዊ ችግሮችን በሠለጠነ መንገድ እንዲፈቱ የሚያደርግ እና ዘለቄታዊ ልማት የሚያስገኝ ነው፡፡
ከዚህ አንጻር እያንዳንዱ ዜጋ ሥነ - ዜጋዊ ባህሪያቱ የጐለበተ መሆን ይኖርበታል፡፡ ለዚህም የመራጮችና የሥነ - ዜጋ ትምህርት የላቀ ሚና በመጫወት ዜጐችን ለማህበራዊ እድገት እንዲነሳሱ፣ ማህበራዊ ተሳትፎአቸውንም በማሳደግ መብትና ግዴታውን በማክበር እና በማስከበር የግልፅነትና የመቻቻል እሴቶችን በማጐልበት ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓቱ መዳበር የሚያበረክተው አስተዋፅኦ ጉልህ ነው፡፡
ይህን ለመወጣትም ሥነ - ዜጋዊ እውቀት ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ረገድ ሁሉም ዜጐች የሀገራቸውን የፖለቲካ ሁኔታ፣ በህግ የተሰጡትን መብቶችና ግዴታዎች፣ የማህበረሰቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስሮች፣ የዜግነት ድርሻቸውን፣ ማህበራዊ ችግሮችንና መፍትሔዎቻቸውን እንዲሁም በህግ የተሠጡትን መብቶችና ግዴታዎችን ጠንቅቀው በማወቅ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ማበርከት ይጠበቅባቸዋል፡፡
ቦርዱ ይህን በመገንዘብ መላው የሀገራችን ህዝቦች ሥነ - ዜጋዊ እውቀት እና ክህሎት አዳብረው በሀገራቸው ዴሞክራሲያዊ ግንባታ ሂደት በንቃት እንዲሳተፉ የሚያደርጋቸው የሥነ ዜጋና የመራጮች ትምህርት በስፋት ለመሥጠት በመንቀሳቀስ ላይ መሆኑ የጉዳዩ አስፈላጊነት ምን ያህል ከፍተኛ እንደሆነ ያመላክታል፡፡
የመራጮች ትምህርት በዋንኛነት ለመራጩ ህዝብ የሚሠጥ ሲሆን ይህም መራጩ ህዝብ ሊያውቀው የሚገባውን መረጃ በቅድሚያ አውቆ በምርጫ እንዲሳተፍ የሚያስችለው ትምህርት ነው፡፡ ትምህርቱ በተለይ እድሜያቸው 18 ዓመት እና ከዚያ በላይ ለሆናቸው ዜጐች እና በምርጫ ለመሳተፍ ብቁ ለሆኑ ዜጐች ስለምርጫ ምንነት፣ ስለምርጫ ጥቅም፣ ስለምርጫ አካሄድና ሥርዓት፣ ስለምርጫ ሂደት ደረጃዎች፣ ስለመራጮች አመዘጋገብ፣ ስለድምፅ አሠጣጥ፣ … ወዘተ የሚማሩበት ነው፡፡
የመራጮች ትምህርት በምርጫ ወቅት በስፋት ቢስጥም እስከ ሚቀጥለው የምርጫ ወቅት ድረስ ህዝቡ ሥነ - ዜጋዊ እውቀቱ እና ክህሎቱን የሚያዳብሩ ተከታታይነት ያላቸው ግንዛቤ ማሳደጊያዎችን በስፋት መሥጠት እጅግ ተመራጭ ነው፡፡ ለዚህም ነው ቦርዱ ከዚህ መሠረታዊ ፅንሰ - ሀሳብ ተነስቶ ለመላው የሀገራችን ህዝቦች የሥነ ዜጋዊ እውቀት እና ክህሎት ማሳደጊያ ትምህርት ለመሥጠት የተነሳሳው፡፡ ስለሆነም የመራጮችና የሥነ - ዜጋ ትምህርት በሀገራችን መሥጠቱ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ትልቅ አስተዋፅኦ ያለውና መራጩ ህዝብ በነጻነት ያለማንም ጣልቃ ገብነት፣ ያለፍርሃት፣ ያለተፅዕኖ እና ከማንኛውም መደለያ ነጻ በሆነ መልኩ ድምፅ በመሥጠት በእውቀት ላይ የተመሠረተ ውሳኔ ለመሥጠት የሚያስችለው ትምህርት ነው፡፡
No comments:
Post a Comment