About Me

My photo
Independence, Neutrality, Rule of the Law, Impartiality and Transparency.

Tuesday, December 13, 2011

የቦርዱን ራዕይ የሚያሳልጥ የአምስት ዓመት ዕቅድ…!


ራዕይ ማለት አንድ አገር፣ ተቋም፣ ድርጅት … ለመጪው መሆን  የሚፈልጉትና በተስፋ የሚጠብቁት ስኬት ነው፡፡ የአገራችን ራዕይ ‘‘በሕዝብ ተሳትፎና በሕዝቦች መፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትና መልካም አስተዳደር የሰፈነባት፣ ማህበራዊ ፍትህ የነገሰባት፣ ከድህነት ተላቃ መካከለኛ ገቢ ያላት ኢትዮጵያን እውን ማድረግ ’’ ይላል፡፡ ይህ ራዕይ በሁለት አስርተ ዓመታት ሊደረስበት የታሰበና የታቀደ ራዕይ ነው፡፡

 

ራዕይ እና ተልዕኮ በባህሪያቸው የሚመሳሰሉ ቢሆኑም የሚለያዩባቸው መንገዶችም አሉ፡፡ ተልዕኮ በዕለታዊ የሚከናወኑ ስራዎችና እያከናወንን የምናሻሽላቸው ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር ነው፡፡ ራዕይ ግን ለመጪው መሆን የምንፈልገውን የሚያሳየን፣ ብርታት የሚሰጠንና ለለውጥ የሚያነሳሳን ነው፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እንደማንኛውም የመንግስት መስሪያ ቤቶች የራሱ የሆነ ራዕይና ተልዕኮ አለው፡፡
ራዕይ፡-
“ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የመምረጥንና የመመረጥ መብታቸውን ነፃ፣ ፍትሃዊ እና ሰላማዊ በሆነ መንገድ ተግባራዊ የሚያደርጉበት ጠንካራ ሕገመንግስታዊ ስርዓት ዕውን ሆኖ ማየት ” ነው፡፡
ተልዕኮ፡-
“ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የህብረተሰቡን የስነ ዜጋ ግንዛቤ በማሳደግ ህዝቡ የመምረጥና የመመረጥ መብቱን በአግባቡ አውቆ ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ቀጣይነት የበኩሉን ሚና እንዲወጣ ማስቻል፤ በሃገሪቱ ሁሉንም ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዕኩልነት ያሳተፈ ፍትሀዊ፣ ነፃና ገለልተኛ ምርጫን በህጉ መሰረት በብቃት ማስፈፀም ” ነው፡፡
ቦርዱ ይህን ራዕይና ተልዕኮ ለማስፈፀም የተለያዩ ስልቶችን በመቀየስ ለተግባራዊነታቸው እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ ከነዚህም አንዱ የቦርዱ የ5 ዓመት ስትራተጂክ ዕቅድ ሲሆን ዕቅዱም ከአገራቸን የአምስት ዓመት የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በመነሳት የተቀረፀ ነው፡፡
ከ 2003 - 2007 ዓ.ም ተግባራዊ የሚደረገው የቦርዱ ስትራቴጂክ ዕቅድ ዋና ዓላማ የቦርዱ አሰራር ከመንግስት የአምስት ዓመት የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ጋር ተጣጥሞ እንዲሄድ በማድረግ፣ እያደገ የመጣውን የባለድርሻ አካላት ፍላጎት ቀልጣፋና ቀጣይነት ባለው ሁኔታ ማሟላት፣ የህዝቡን እርካታ መጨመር እና ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የምርጫ አሰራር ለመዘርጋት እንዲያስችለው ለማድረግ የተዘጋጀ ነው፡፡
ይህ የአምስት አመት ስትራቴጂክ እቅድ ቦርዱ ያከናወናቸውን አጠቃላይ እንቅስቃሴዎች እና አሁን የሚገኝበትን ሁኔታ በመገምገም የተዘጋጀ ሲሆን በቀጣይ አምስት አመታት ገራችን ለምታካሂደው የዲሞክራሲ ስርአት ግንባታ የራሱን ገንቢ ሚና ለመጫወት እና ከቦርዱ የሚጠበቁ ስራዎች በብቃት ለመወጣት የሚያስችለው አጠቃላይ አቅም የሚፈጥር ነው፡፡ ሀገሪቷን በ2015 መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገሮች ተርታ ለማሰለፍ የተቀመጠውን ራእይ ለማፋጠን የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ተዘጋጅቶ ለማስፈጸም ልዩ ትኩረት ከሚሹ ዘርፎች መካከል የመልካም አስተዳደር እና የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ አንዱ ዘርፍ እንደሆነም በዕቅዱ ተመልክቷል፡፡
ሀገራችን አሁን የደረሰችበት የእድገት ደረጃ ባለፉት አመታት የተከናወኑ የዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር ስርአት ግንባታ ውጤት ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ የሀገራችን የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን እቅድ እውን ለማድረግና የልማት ሂደቱን በቀጣይነት ለማረጋገጥ ከመቼውም በላቀ መልኩ ተቀናጅቶ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ ምርጫ የዴሞክራሲ ስርአት ዋናው ምሶሶ በመሆኑ ዜጎች በመረጧቸው አስተዳዳሪዎች የመመራት ሕገመንግሥታዊ መብታቸውን የሚያረጋግጡበት ብቸኛ መሣሪያ ነው፡፡ ስለሆነም ዜጎች ይህንን መብታቸውን በተሟላ መልኩ ለማስከበር የምርጫ  እንቅስቃሴዎችን ተአማኒነቱና ተቀባይነቱን በባለድርሻ አካላት በተለይ ደግሞ በመራጩ ህዝብ ዘንድ በቀጣይነት ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ በመሆኑም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በመልካም አስተዳደር፣ በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ እንዲሁም በሕዝብ ተሳትፎ ዙሪያ የበኩሉን ድርሻ ለመወጣት ራዕዩን ሰንቆ እየሰራ ይገኛል፡፡
የቦርዱ ስትራተጂክ ዕቅድ ለማዘጋጀት የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ እንደተጠበቀ ሆኖ ሌሎችም ታሳቢ የተደረጉ ጉዳዮች አሉ፡፡ እነዚህም የቦርዱ የ2002 ዓ.ም በጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት እና የ2003 ዓ.ም በጀት ዓመት ዕቅድ፣ ቦርዱ በመላ አገሪቱ ያካሄደውን የ2002 ዓ.ም የድህረ ምርጫ ግምገማ፣ ከባለድርሻ አካላት የተደረገ ውይይት እና የተሰጠ አስተያየት፣ ከፅሕፈት ቤቱ ሰራተኞች ጋር የተደረገውን ውይይት ይገኙበታል፡፡
ከዚህ በመነሳትም ቦርዱ ለተቋሙ ብሎም ለአገሪቱ ውጤታማነት አስፈላጊ የሆኑ ስድስት ቁልፍ ስትራቴጂካዊ ጉዳዮችን ያካተተ ስትራተጂክ ዕቅድ አዘጋጅቷል፡፡ እነዚህ ቁልፍ ስትራቴጂካዊ ጉዳዮች፦
Ø  ጠንካራ የሃብት ጥበቃና ክትትል ስርዓት እንዲኖር ማድረግ፣
Ø  የሰራተኛ የመፈፀም፣ የማስፈፀም ዓቅምና ተነሳሽነት እንዲጠነክር ማድረግ፣
Ø  የቦርዱን የመረጃ አያያዝ፣ አጠቃቀምና ፍሰት የተጠናከረ እንዲሆን ማድረግ፣
Ø  መራጩ ህዝብ በቦርዱ አሰራር ላይ በቂ ዕውቀትና ግንዛቤ እንዲኖረው ማድርግ፣
Ø  ወቅታዊውን የህዝብ ብዛት ያገናዘበ የምርጫ ክልል አከላለል እንዲኖር ማድረግ፣
Ø  ሴቶች በምርጫ አስፈፃሚነትና በተመራጭነት ያላቸው ተሳትፎ ማሳደግ የሚሉት ናቸው፡፡
እነዚህን ቁልፍ ስትራተጂክ ጉዳዮችና እና ሌሎች ክንውኖች በዚህ አምስት ዓመት የቦርዱ ስትራተጂክ ዕቅድ መካተታቸው ተቋሙ በመጪው አምስት ዓመት በጣም የተሻለ ስራ ለመስራት ያግዛል፡፡ ከዚህ አልፎም ቦርዱ የሰነቀውን ራዕይ የሚያፋጥንና የሚያሳልጥ ይሆናል፡፡




No comments: